መልከ ጼዴቅ፡ ማን ነው?
ራሱን፡ “የሰው ልጅ” እያለ የሚጠራው፡ የእግዚአብሔር ልጅ የኾነው፡ ዘለዓለማዊው ካህንና እውነተኛው ንጉሥ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ በመጨረሻው የሕይወት ዘመን እስኪገለጥ ድረስ፡ “መልከ ጼዴቅ” እና “ንጉሠ ሳሌም”፡ የልዑል እግዚአብሔር ካህንና የሰላም ንጉሥ፡ በሚል ስያሜ፡ የእርሱ ምሳሌ ኾኖ፡ በምድር ላይ የሚታይ፡ አንድ ደግ ሰው፡ ከኖኀ ዘመን አንሥቶ፡ በሰዎች መካከል፡ በተከታታይ፡ በኢየሩሳሌም፡ እየተሠየመ ይኖር ነበር።
በዚህ ማዕርግ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ከተቀመጡት አጼዎች መካከል፡ ዝክረ ነገራቸው፡ በቅዱሳንና በቅዱሳት ልቦና ተመዝግቦ፡ በይበልጥ የሚነበበውና በእነዚሁ አንደበት የሚነገረው፥ እንዲሁም፡ በየዘመናቸው፡ እንግዳ የኾኑ፡ የእግዚአብሔር ድንቃድንቅ ድርጊቶች ስለተፈጸሙ፡ ስማቸው፡ በገናንነት የሚጠራው፡ ሦስቱ ናቸው፤ እነዚህም፡ “ኢትዮጲስ”፡ በማዕረግ ስሙም፡ “መልከ ጼዴቅ” የተባለውና ሚስቱ፡ “እንተላ” የተባለችው፥ ከኖኅ፡ የቅዱሱን ኪዳን ሕያው ቅርስ፡ በውርስ የተረከበውና ኢየሩሳሌምን የቈረቈረው፡ የመጀመሪያው መልከ ጼዴቅ ነው።
የመጀመሪያው መልከ ጼዴቅ፡ ይኸው ኢትዮጲስና ይህችው ሚስቱ፡ እንተላ፡ የመጨረሻውንና ዘለዓለማዊዉን፥ አማናዊዉንም መልከ ጼዴቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በወለዱት፡ በመለኮታዊው አባቱ፡ በእግዚአብሔር አብና በሰብአዊት እናቱ፡ በድንግል ማርያም ተመስለዋል።
ይኽው ቀዳማዊው መልከ ጼዴቅ፡ የቅዱሱ ኪዳን የመጨረሻ ማኀተም ለኾነው፡ ለክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም፡ አርአያ ኾኖ በቆየው፡ በኅብስትና በጽዋው የቃል ኪዳን ምልክትነት፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፡ ቤተ ሕዝብነትን፥ ሥልጣነ ክህነትንና በትረ ምልክናን አዋሕዶ ይዞ፡ አገልግሎቱን ሲያበረክት ኖርዋል፤ ይኽም አገልግሎት፡ ከትውልድ ወደትውልድ ሲተላለፍ ቆይቶ፡ በመካከለኛው መልከ ጼዴቅ አማካይነት፡ ከመጨረሻው መልከ ጼዴቅ ደርሷል።
መካከለኛው (ኹለተኛው) መልከ ጼዴቅም፡ (በድንግልናዊነቱና በብሕትውናውም፡ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌው የኾነለት)፡ እንዲሁ፡ እንደመጀመሪያው፡ የተቀደሰና የበቃ ሰው ስለነበረ፡ ቀድሞ፡ ጣዖት አምላኪ ለነበረው፡ ለአብራም፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን፥ የሃይማኖትንና የምግባርንም ሥርዓት ካስተማረው በኃላ፡ “ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ፡ ለልዑል እግዚአብሔር፡ የተባረክህ ነህ!” ብሎ፡ አብርሃምን በመመረቅ፡ የኢትዮጵያዊነት፡ አንዱ መታወቂያ በኾነው፡ በግርዛት ምልክትነት፡ ለእውነተኛው መለኮታዊው ቃል ኪዳን ያበቃውን፡ የእግዚአብሔር በረከት፡ በአብርሃም ላይ እንዲያድርበት አድርጓል።
የመጨረሻውና አማናዊው መልከ ጼዴቅም፡ የምሕረት ጸጋውን፡ በሥጋውና በደሙ ቃል ኪዳን፡ ለፍጥረቱ ኹሉ፡ ለአንዴና ለመቼውም ጊዜ፥ ለዘለዓለሙም ሰጠ። እርሱም፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
መለኮት በተዋሀደው ትስብእቱ (በአምላካዊው ሰውነቱ) ምክንያት፡ የተስፋውና የትንቢቱ፥ የምሳሌውም ፍጻሜ፥ ዘለዓለማዊው ካህንና አማናዊው (እውነተኛው) የሰላም ንጉሥ ከኾነው፡ ከመጨረሻው መልከ ጼዴቅ በፊት ያሉት፡ ከላይ የተገለጡት፡ እኒህ፡ የመጀመሪያውና የመካከለኛው መልከ ጼዴቆች (አጼዎች)፡ በመለኮታዊው መንግሥት ውስጥ፡ ቤተ ሕዝብነትን፥ ቤተ ክህነትንና ቤተ ምልክናን አውሕዶ ለሰጣቸው፡ ለፈጣሪያቸው፡ እግዚአብሔር፡ ምስጋናቸውን ያቀረቡበት፥ ጸጋውን ይቀበሉበትና በረከቱን ያስተላለፍበት የነበረው፡ የቅዱሱ ኪዳን የዘወትር ምልክታቸው፡ የመሶቡ ኅብስትና የጽዋው መጠጥ ነበር።
ይኽን፡ የቃል ኪዳን ምልክት የኾነውን፡ የመሶቡን ኅብስትና የጽዋውን መጠጥ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ለሰብአዊ ሕይወታቸው ደኅንነትና ለማኅበራዊ ኑሮአቸው አንድነት፡ መገለጫ ይኾን ዘንድ፡ የግልና የቤተሰብ፥ የማኅበርና የኅብረተሰብ፥ የሃይማኖትና የአገር በዓሎቻቸውን ያከብሩበታል። እርሱንም፡ “ጠበል ጠዲቅ”፡ ማለትም፡ “ጸበለ መልከ ጸዴቅ”፡ “የመልከ ጸዴቅ በረከት” እያሉ፡ ዳቦውን በመሶብ፥ መጠጡን በጽዋ አዘጋጅተው በማቅረብ፥ ያንንም፡ በጥልቅ ሃይማኖታዊ ስሜት ኾነው፡ በእግዚአብሔር ስም፡ ጸሎት አድርገው በመሳተፍ፡ ምስጋናቸውን ያቀርቡበታል፤ መንፈሳዊና ሥጋዊ በረከትንም፡ ከእርሱ ይቀበሉበታል።
ኢትዮጵያውያን፡ ይኽን ሥረዓት ሳያቋርጡ እየፈጸሙ የሚኖሩት፡ መልከ ጸዴቅ፡ ለሥጋዊው የኢትዮጵያዊነት ትውልዳቸው፡ ግንዱ አባታቸው በመኾኑ ብቻ ሳይኾን፡ ከእግዚአብሔር፡ በቃል ኪዳን ለተቀበላቸው፡ ለመንፈሳውያኑ ጸጋዎች፡ የእርሱ፡ ቀጥተኛ ወራሾች መኾናቸውንም ለማስታወስና ለማረጋገጥ ነው። ይኽውም፦
፩ኛ፦ የእግዚአብሔር፡ የቃል ኪዳን ወገን ለመኾን ለሚያበቃው፡ ለኢትዮጵያዊው ሰውነት፡ የዘር ግንድ በመኾን፡ የቤተ ሕዝቡን፥ ፪ኛ፦ “የልዑል እግዚአብሔር ካህን” በሚል ማዕረግ ተሠይሞ፡ የቤተ ክህነትን፥ ፫ኛም፦ “እውነተኛው የሳሌም (የሰላም/ የኢየሩሳሌም) ንጉሥ” ተብሎ በመቀባት፡ የቤተ ምልክናን ባለመብትነትና ባለቤትነት፡ ባጠቃላይ፡ ለሰው ልጆች ኹሉ፥ በተለይም፡ ቃል ኪዳኑን አምነው ለተቀበሉት ኢትዮጵያውያን ለማቀዳጀት የሚያበቃውን ጸጋ ያሰገኘ፡ ይኽው መልከ ጼዴቅ መኾኑን እያረጋገጡ ያበሥራሉ። “ሳሌም”፡ የሚለው፡ የግእዙ፡ የቃል ለቃል ትርጉም፡ “ሰላም” ማለት ሲኾን፡ “ኢየሩሳሌም” ወይም፡ “ሀገረ ሰላም” የሚለው ስያሜ፡ ከዚያ ተገኝቷል።
(ለተጨማሪ ማብራሪያ ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ! ከገጽ ፷፭ ጀምሮ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፡ አንደኛ መጽሓፍ፤ ከገጽ ፩፻፲፮ ጀምሮ፤ በተጨማሪ፡ ከጥያቄና መልስ ማሕደር፡ ከወ/ሮ ፍቅርተ ለተጠየቀ ጥያቄ፡ የተሰጠውን የመጀመሪያ እ-ጦማር ምላሽ፡ ከገጽ ፬ ጀምሮ ይመልከቱ)