በየካቲት ወር፥ ፳፻፰ ዓ.ም. ዓመታዊው፡ የኪዳነ-ምሕረት በዓላችንና የጾመ ኢትዮጵያ ምሕላችን ማብቂያ፡ ዐብረው በዋሉበት፡ ቅድስትና የተለየች፥ የተመረጠችና የተገለጠች ዕለት በኾነችው፡ ኪዳናዊት፡ የካቲት ፲፮ ቀን የተከሠተ፡ ተኣምራዊ፡ የሥነ-ፍጥረት ትንግርት።

ዮም ፍሥሓ ኮነ!
በእንተ ኢትዮጵያ፡ እግዚአብሔር-እም፡ ድንግል ማርያም፣
ዘታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔርናሃ፡ እንበይነ ፍጥረተ-ዓለም፥
ወበእንተ ኢየሱስ መሲሕ ኢትዮጵያዊ፡ ዳግማይ አዳም፣
ውእቱ አንበሳ፡ እምነገደ ይሁዳ፡ ዘሞኦ ለአርዌ ነዓዊ ዘገዳም፣
እሉ እሙንቱ፡ ዘጸገዉነ ኪዳነ ምሕረት ዘሰብዓቱ ማኅተም።

ዛሬ፡ ደስታ ኾነ!
ስለፍጥረተ-ዓለሙ ድኅነት፡ ትስብእታዊ እጆቿን፡
ወደመለኮታዊው እግዚአብሔርነቷ በዘረጋችው
በኢትዮጵያ፡ እግዚአብሔር-እም፡ ድንግል ማርያምና፣
ነጣቂው የዱር አውሬ የኾነውን ሰይጣንን ባሸነፈው፡
በዳግማዊው አዳም፡ በኢትዮጵያዊው ኢየሱስ መሲሕ ምክንያት፣
እርሱም፡ ከይሁዳ ነገድ የተገኘው፡ ድል አድራጊው አንበሳ ነው!
እኒሁ፡ እናትና ልጅ፡ ባለሰባት ማኅተም የምሕረት ኪዳንን፡
የሰጡንና ያስገኙልን ናቸው።

 

ይድረስ፦ ለኪዳናውያት እኅቶቼና ለኪዳናውያን ወንድሞቼ!

     ቸሩ ፈጣሪያችን፡ በየካቲት ፲፮ ቀን፥ ፳፻፰ ዓ. ም. የታወጀውን፡ "በዓለ-ኢትዮጵያ"ን፡ ወደፊትም፡ በጊዜው እናከብረው ዘንድ፡ ለዚያን ጊዜ እስከሚያበቃን፡ ቡሩኩን ጾመ-ኢትዮጵያን፡ እንኳን፡ በሰላም አስፈጸመን፤ ቅዱሱን በዓለ ኪዳነ ምሕረትንም፡ እንኳን፡ በሓሤት ለማክበር አበቃን!

     ይህን፡ ልዩ እ-ጦማር የጻፍሁላችሁ፡ ለምን እንደኾነ፡ ምክንያቱን ልግለጽላችሁ!

     ኹላችሁም እንደምታውቁት፡ በ"ጾመ-ኢትዮጵያ" እና በ"ሰላም፡ ለኢትዮጵያ" ስሞች፡ በየመንፈቀ ዘመኑ፡ ለአርባ ዓመታት ሲካኼድ የቆየው፡ የምሕላና የንስሓ ሱባኤያችን፡ ያስገኘውን፡ ፍሬያማውን የምሥራች ዘለዓለማዊ ዜና የያዘው፡ ዐሥራ አንደኛው ቃለ-ዐዋድ፡ በየካቲት ፲፮ ቀን፥ ፳፻፰ ዓ. ም. ከሳምንቱ፡ የመጀመሪያው የፀሓይ መዓልት በኾነው፡ በዕለተ ረቡዕ፡ ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት መታወጁ ይታወሳል። ይኸው ቀን፡ የዘንድሮው፡ ዓመታዊው የኪዳነ-ምሕረት በዓላችንና የጾመ ኢትዮጵያ፡ ምሕላችን ማብቂያ፡ ዐብሮ የዋለበት መኾኑም፡ በኹላችንም ዘንድ ይታወቃል።

     ይህ ድንቅ ነገር የኾነው፡ በመለኮታዊው ዕቅድ፡ ታስቦበትና ታውቆ፥ ተዘጋጅቶና ተከናውኖም በተፈጸመ ሥርዓት እንጂ፡ እንደሰዎች ልማዳዊ አነጋገር፡ እንዲያው በ"አጋጣሚ" አለመኾኑ፡ በቅዱሱ ኪዳን፡ "የኢትዮጵያ ልጆች" ዘንድ የታመነ ነው። ከእኒሁ፡ "የኢትዮጵያ ልጆች" መካከል፡ እኔም፡ አንዱ ስለኾንሁ፡ በዚሁ፡ በየካቲት ፲፮ ቀን፥ ፳፻፰ ዓ. ም. የኾነውንና እራሴ በዓይኖቼ ተመልክቼ፡ ያረጋገጥሁትን፡ እንደተአምር የሚቆጠር፡ የሥነ-ፍጥረት ድርጊትን ስላየሁ፡"ይህን የተፈጥሮ ትንግርት፡ ለእናንተም ላካፍላችሁ!" ብዬ ነው።

     ትንግርቱ፡ እርግጥ፡ የእኛን፡ የእያንዳንዳችንን፡ ኪዳናዊ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ እምነታችንን የሚያጠናክር ሊኾንልን እንደሚችል ቢታወቅም፡ መልእክቱ፡ ለእኛ፡ ላመንነው፡ "የኢትዮጵያ ልጆች" ሳይኾን፡ ለማያምኑት ወገኖች፡ ከተጐዱበት የእምነት ድክመታቸው ወጥተው፡ ወደእውነተኛዋ የቅዱሱ ኪዳን ሃይማኖታቸው ለመድረስ እንዲያግዛቸው ለማድረግ መኾኑ፡ ጥርጥር የለውም። ይኸውም፡ እንዲህ ነው፡- እኔ፡ በሱባኤ በአቴ ውስጥ፡ ተገቢ ምግባሬን እያካኼድሁ ነበርሁ። ከዚህ ቀደም ብዬ ግን፡ በማለዳው ሰዓት፡ እንዳስለመድሁት፡ ከክፍሌ ወጣ ብዬ ስለነበረ፡ እንደሰሞኑ ኹሉ፡ ሰማዩ ጠርቶና የፀሓይዋ ብርሃን፡ በዓለሙ ኹሉ፡ በደማቅ ኹኔታ መልቶ እንደነበረ ተመልክቼ፡ ተመልሻለሁ። እንደተመለስሁም፡ ባጭር ጊዜ ውስጥ፡ ያ፡ ያልነበረው የዝናም ደመና፡ በእኔ አካባቢ ባለው ጠፈር ላይ፡ [በሌላውም አካባቢ፡ እንዲሁ ኾኖ እንደነበረ አላውቅም]፡ ምንጊዜና እንዴትስ እንደተሰባሰበ ልገምተው ባልቻልሁበት ኹኔታ፡ ተከማችቶ ኖሮ፡ ከበድ ያለና ጠል የበዛበት የዝናም ውኃ፡ በቆርቆሮ ቤቴ ላይ፡ ድንገት ሲወርድ ሰማሁ፤ በድምፁ ተደናግጬ፡ ራሴን፡ ከተግባሬ ቀና ሳደርግ፡ በደመቀ የፀሓይ ብርሃን ውስጥ እያብረቀረቀ የሚወርድ፡ ልዩ ዓይነት ዝናም መኾኑን፡ በኹለቱም የመስታወት መስኮቶቼ በኩል አስተዋልሁ።

     በእውን የማየውን፡ ይህን እውነታ ማመን አቅቶኝ፡ ያን የመሰለ የፈካ የፀሓይ ብርሃን፡ እንዲያ እያበራ እያለ፡ ይህን የሚያህል ከባድ ዝናም ዐብሮ ሲዘንብ ስላየኹ፡ ወዲያው፡ ከመቀመጫዬ ተነሥቼ፡ ከክፍሌ ወጣሁ፤ በፊተኛው ታዛዬ ላይ ቆሜ፥ ወዲያ ወዲህም እያልሁ ወደሰማይ ስመለከት፡ ፀሓይዋ፡ በዝናሙ ደመና ተሸፍና እያለች፡ ያን የሚያህል አንፀባራቂ ብርሃን መታየቱ፡ እጅግ አስገርሞኝ፡ ወደበአቴ ተመለስሁ። በዚህ መልኩና ይዘቱ፡ ዝናሙ፡ ለተወሰነ ጊዜ ከቀጠለ በኋላ፡ ቢያባራም፡ መዓልቱንና ምሽቱን፡ ዐልፎ ዐልፎ፥ በተከታዩ ሌሊትና በነግሁ ሰዓቶች ጭምር፡ ይኸው ዝናም፡ በለሰለሰና በሠመረ አወራረዱ፡ አኹንም፡ በእያግጣጫው፡ ጐልተው ከሚታዩ ቀስተ ደመናዎች ጋር መጣሉንና ማረስረሱን አላቋረጠም።

     እኔም፡ በአንክሮና በተዘክሮ መንፈስ ተመሥጬ፡ "እንዴ! ይህ ምልክት፡ በዚች በዛሬዋ የተለየች ቀን፡ በእግዚአብሔር እም ኢትዮጵያ ድንግል ማርያም አንደበት፡ ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት የታወጀው፡ የይቅርታና የምሕረት ዐዋጅ፡ የጸና መኾኑን፡ ለፍጥረታተ-ዓለማቱ ሊያመለክት፡ ከፈጣሪ የታዘዘ ይኾን?" ብዬ አሰብሁ፤ በቃሌም፡ ይህንኑ ትንግርት ላዩ ቤተሰቤ፡ እንዲሁ ተናገርሁ። ይህን የተፈጥሮ ትንግርታዊ ምልክት፡ ምናልባት፡ በብርሃናዊ ሥዕል የቀረፀ፡ አንዳች ሰው ሊኖር ይችላልና፡ በየበኩላችሁ፡ መጠበቁና መከታተሉ አግባብ ይኾናል። የማያቋርጠው ኪዳናዊ ምስጋናችን፡ በያለንበት፡ ለቅድስት ሥላሴ ይድረሳቸው!

ኪዳናዊ ወንድማችሁና የክህነት [የአገልግሎት] ባልደረባችሁ ፦ ንቡረ-እድ ኤርምያስ።