በፌስ ቡክ የውስጥ መሥመር በኩል፡ በቅርቡ፡ በእስላሞች ሠይፍ የታረዱትን፡ የቅብጥ ክርስቲያኖች አስመልክቶ፡ ለክህነታዊ ባልደረባችን ለተላከ ወቅታዊ መልእክት፡ የተሰጠ ምላሽ።
ለክህነታዊ ባልደረባችን የደረሳት መልእክት።
ሰሞኑን የ"አይሲስ" / ISIS / "ኢስላማዊ አሸባሪ ቡድን": በጌታችንና መድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስና፥ በቅዱስ መስቀሉ ላይ ተገዳድሮ የገደላቸውን 'ሃያ አንድ የግብፅ ክርስቲያኖችን' ስመለከት፤ አንድ ቀን ያየሁት ራእይ ትዝ አለኝና ለጋሽዬ ልንገራቸው ብዬ ነው::
እለቱና ቀኑም: ጥቅምት ሃያ ሰባት ቀን: ኹለት ሺህ አራት ዓመተ ምሕረት ነበር:: ( ፳፯/ዐ፪/፳፻፬ ዓ.ም. )
ይኼውም: እኔ ከኾነ ቤት ወጥቼ ስመለከት፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ቀራኒዮው ሁሉ በመስቀል ላይ በችንካር ተሰቅሎ ነበር፤ ነፍሱም ከሥጋው አልተለየችም ነበር::
ጠመንጃ የታጠቁ እስላም ሰዎችም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ በመሳሪያ ተኩሰው ለመግደል ሲሞክሩ ያየኋቸው ይመስለኛል:: በአጠገቡም ኢየሱስ ክርስቶስን የሚረዳው ሰው አንድም አልነበረም::
ከዚያም አንድ መሳሪያ የያዘ እስላም ሰው የጠመንጃውን አፈሙዝ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዙሮ ሊገድለው ይሞክራል፥ ግን አልተኮሰበትም፤ ኢየሱስ ክርስቶስን ሊገድሉት የሚፈልጉበት ምክንያትም፥ "ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎና ሞቶ መነሳቱን ሰዎች እንዳያምኑ፥ በሦስተኛውም ቀን እንዳይነሳ ከመፈለጋቸው የተነሳ እንደነበር" ይመስለኛል:: ሌሎቹ የእስላሙ ሰራዊትም በሩቅ ኾነው የኢየሱስ ክርስቶስን ደጋፊዎች /ክርስቲያኖቹን/ ያሳድዳሉ፥ ወደ እርሱም እንዳይቀርቡ ክርስቲያኖቹን ይከለክሏቸዋል:: ለእኔ ግን ከኢየሱስ ክርስቶስና ከጠመንጃ ያዡ ሰውዬ በቀር በተሰቀለበት ማንም አይታየኝም ነበር::
በመጨረሻም: ኢየሱስ ክርስቶስን በመሳሪያ ተኩሰው እንዳይገድሉት ለማዳን ብዬ በብስጭትና በቁጣም ኾኜ ጠመንጃ ያዡ ሰውዬውን ለማባረር እኔ ድንጋይ እወረውርበታለሁኝ፤ በቃሌም እንዲህ ስል እናገራለሁ:- "አኹንማ ምን ታደርጉ?፤ ጊዜው የእናንተ ነው!፤ መሳሪያም ይዛችኋል!፤ የፈለጋችሁትን ልታደርጉ ነው" እላቸዋለሁ::
ደግሞ የገረመኝ ጠመንጃ የያዘው ሰው ላይ ድንጋይ ስወረውርበት: ወደኔ ይተኩስብኛል ብዬ በፍጹም አልፈራም ነበር፤ እርሱም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስና በሩቅ ወዳሉት ወዳባረራቸው ክርስቲያኖች እንጂ ወደኔ አይመለከትም፤
ሌሎቹ የእስላሙ ሰራዊት /የጠመንጃ ያዡ ባልደረቦቹ/ ደግሞ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳይቀርቡ ክርስቲያኖቹን እያሳደዷቸው ይመስለኛል፤ እነዚያም ክርስቲያኖቹ ደግሞ እነዚህን የእስላም ሰራዊት መቋቋም ስላልቻሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጠጋትና ኢየሱስ ክርስቶስን ማዳን አልቻሉም::
ጠመንጃ ያዡም ሰውዬ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳን እንደምከለክለው ያወቀ ይመስለኛል፤ ነገር ግን እኔን እንደ እነዚያ ክርስቲያኖቹ ሊያባርረኝ አልሞከረም::
ከእንቅልፌ ስነቃም: ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ፤ ያኔ "እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሐንስ በአጠገቡ ነበሩ፤ አኹን ግን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በአጠገቡ ማንም የለም" አልኩኝ::
ክርስቲያኖቹ ሕዝቦችም: የኢትዮዽያ ክርስቲያኖች አይመስሉኝም የውጭ አገር ክርስቲያን እንጂ::
ከንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ የተሰጠ ምላሽ።
ለኪዳናዊት እኅቴ! በፍቅረ እግዚአብሔር፡ ሰላም እልሻለሁ፤ በላክሽልኝ እ-ጦማር አማካይነት፡ ደኅንነትሽን ስላወቅሁ፡ ደስ ብሎኝ፥ ኹላችንንም፡ በያለንበት የሚጠብቀንን፡ ቸሩ ፈጣሪያችንን፡ ከነእናቱ አመሰገንሁ።
ኪዳናዊ ወንድማችን የላከልን መልእክት፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት በኩል እየተላለፈ ያለውን መልእክትና እየተፈጸመ ያለውን ተልእኮ፡ በበለጠ የሚያረጋግጥና የሚያጠናክር ነው። ለእኛ፡ ይህ ኹሉ ድርጊት፡ እንደእንግዳ ነገር ተቆጥሮ የሚያስደነግጠንና የሚያስደንቀን አይደለም። የሚጠበቅ ነውና። ከመለኮታዊው መምህራችንም፡ አስቀድሞ ተነግሮናል። ለበቃው ባለራእይ፡ አስቀድሞ እንደታየው ኹሉ፡ ዛሬ፣ በመስቀሉ ላይ፡ ራሱን ሕያው አድርጎ እየተናገረ ያለው፡ ኢትዮጵያዊው ኢየሱስ መሢሕ፡ ከእርሱ፡ ከታማኙ ኪዳናዊ አገልጋዩ ብቻ በቀር፡ ማንም ዐብሮት እንደሌለ፥ ነገር ግን፡ ባለጠመንጃው፡ እንኳንስ የተሰቀለውን ጌታ ቀርቶ፡ ስለእርሱ የሚከላከለውን ኪዳናዊ አገልጋይ እንኳ፡ በምንም መንገድ ሊጎዳ እንዳልቻለ፡ ያው በገሃድ ታይቷል፤ በባለራእዩም ተነግሯል። አዎን! ራእዩም፥ ድርጊቱም፥ ኹሉም፡ አረጋግጠው የሚያሳዩት፡ በአኹኑ ጊዜ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘንድ፡ እየተካኼደ ያለውን እውን ኹኔታ አግዝፎ የሚያሳውቅ ምልክት ነው።
በዓለም ላይ "ክርስቲያን ነኝ!" የሚለው ወገን፥ የግብፅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ፡ "በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኩኝ!" ብሎ፡ የሃይማኖትና የምግባር መመሪያ ሥርዓትን፡ በተሰቀለ ሥጋውና በፈሰሰው ደሙ ዐትሞ በሰጠው፡ በራሱ፡ በኢየሱስ መሢሕና በቅድስት እናቱ ላይ፡ ምን ዓይነቱን የግብዝነት ድርጊትን እየፈጸሙ እንደኾኑ፡ ፍጥረተ ዓለሙ ኹሉ የሚያውቀው አይደለምን? ታዲያ! በእግዚአብሔር ላይ እየተፈጸመ ያለው፡ ይህን የመሰለው ግብዝነት፡ "ውጤቱ፡ ምን ይኾናል!" ተብሎ ኖርዋል የተጠበቀው? ለዚህ ነው፡ ለባለራእዩ፡ ቀደም ብሎ የተገለጠው፡ ይህ አሠቃቂ ድርጊት፡ ዛሬ፡ ገሃድ ኾኖ ሲፈጸም፡ ለኪዳናውያንና ለኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆች አያስደንቅም! አያስገርምምም!" ያሰኘው።
እንዲያውም፡ በዚህ ጊዜ፡ ለዚህ አሠቃቂ ኹኔታ፡ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት የምታስተላልፈው መልእክት ቢኖር፡ በቅርቡ፡ በጾመ ኢትዮጵያ ያደረገችውን በመድገም ይኾናል፤ ይኸውም፡ "ወይስ፡ ይህ ኹሉ፡ ለምን እንደኾነ የሚያውቀው፡ እርሱው፡ ፈጣሪያችንና መድኃኒታችን፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ዛሬም፡ በመንፈስ ቅዱስ፡ "በዚያ ወራት፡ ሰዎች፡ ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥተው፡ [በዚያን ጊዜ፡] ጲላጦስ፡ ደማቸውን፡ ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለቀላቀለው፡ ስለገሊላ ሰዎች፥ [በአኹኑ ጊዜም፡ በግብፅ አገር፡ በእስላሞች ሠይፍ ስለታረዱት ክርስቲያኖች] ነገሩት።
"እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ 'ይህች መከራ ስላገኘቻቸው፡ እነዚህ ገሊላውያን [በአኹኑ ጊዜም፡ እነዚህ የግብፅ ክርስቲያኖች]፡ ከቀሩት፡ የገሊላ [የግብፅ] ሰዎች ኹሉ ይልቅ ተለይተው፡ ኃጢኣተኞች የኾኑ ይመስላችኋልን? አይደለም፤ እላችኋለሁ! እናንተም፡ ንስሓ ካልገባችሁ፡ ኹላችሁ፡ እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ።
"ወይስ፡ እነዚያ፡ በሰሊሆም፡ ግንብ ተጭኖ የገደላቸው፡ ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች፥ [ወይም፡ በአኹኑ ጊዜ፡ እነዚህ ሃያ አንዶቹ፡ የግብፅ ክርስቲያኖች]፡ ከቀሩት፡ የኢየሩሳሌም [የግብፅ] ሰዎች ይልቅ ተለይተው፡ ኃጢኣተኞች የኾኑ ይመስላችኋልን? አይደለም፤ እላችኋለሁ! እናንተም፡ ንስሓ ካልገባችሁ፡ ኹላችሁ፡ እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ።" ስለዚህ፡ የማይቀረው፡ አይቀርምና! በያለንበት፡ በእየተልኳችን እንጠናከር!። (ሉቃ. ፲፫፥ ፩-፭።)
በቅድስት ሥላሴ ስም፡ በዚህ አጋጣሚ፡ ለኪዳናዊ ወንድሜ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። በያለንበት፡ "የተባረከ ዓቢይ ጾም!" ይኹንልን!