ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት መኾኗን፡ ኢትዮጵያውያንም፡ የቅዱሱ ኪዳን ሕዝብ ስለመኾናቸው፡ እስከዛሬ የቀረበውና ወደፊትም የሚቀርበው የጽሑፍ ማስረጃዎች ምንጭ፡ ከየት ነው?
ልኡል እግዚአብሔር፡ በመልኩ በፈጠረው ሰብኣዊ ፍጡሩ ልቦና ውስጥ፡ ያሳደረው፡ ፍጹም እግዚአብሔራዊ እውቀትና በልቡ ጽላት ላይ ጽፎ ያስተማረው፡ ፍጹም እግዚአብሔራዊ ትምህርት አለ። ይኽ እውቀትና ትምህርት፡ በስነፍጥረታዊው የመለኮት ጥበብ፡ የተፈጸመ ትንግርትና በአምላካዊ ቸርነት የተደረገ የቃል ኪዳን ፍሬ ነው። ከዚኽ እውቀትና ትምህርት የሚበልጥ፡ የፍጡር እውቀትና ትምህርት ከቶ የለም። የዚኽ ተፈጥሮዋዊ ጸጋና ዘለአለማዊ በረከት፡ ተቀባይና ባለቤት ከኾነው ከራሱ ከእያንዳንዱ ሰው በኩል፡ ቢዘኽ ረገድ የሚጠበቅና የሚፈለግ በነፍስ ወከፍም ሊፈጸም የሚገባ፡ አንድ ብቸኛ የግዴታ ድርሻ አለ። ይኽም፡ ከፈጣሪው በልግስና የተሰጠውን ይኽንንው የልዕልና ዘውድ፡ በብቅዓት መቀዳጀትና ባህሪው የኾነውን የዚኽን ብልጽግና ተክል ኮትኩቶ ማሳደግ፡ ለበጎ ጥቅምም ማዋል ነው።
ይኽን እውነታ፡ ቸሩ እግዚአብሔር፡ አስቀድሞ በዘመነ ብሉይ በነብያት ባወጀው፡ እንዲኽ በሚለው ቃሉ ገሃድና እውን አድርጎታል።
“…ሎጆችሽ ኹሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ናቸው። ከዚኽ የተነሳ እኒኹ ልጆችሽ በፍጹም ሰላም ይኖራሉ።”
ደግሞ፡
“…ህጌን በልቦናቸው አሳድራለሁ። በህሊናቸውም እጽፈዋለሁ። እንግዲህ ወዲህ አውቀውት እንዲጠብቁት አደርጋቸዋለሁ። እኔ የፍቅር አባት እኾናቸዋለሁ። እነርሱም የፍቅር ልጆቼ ይኾኑኛል። ከዚኽ በኻላ አንዱ ለአንዱ፡ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ ወንድሙን የሚያስተምር፡ አንዱም ለአንዱም ባልንጀራውን የሚያስተምር የለም። ታናናሾቹም ታላላቆቹም፡ ኹሉም ያውቁኛልና።
ኻላም፡ በዘመነ አዲስ፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ከድንግል ማርያም በመወለድ፡ ሰው ኾኖ ወደዚኽ ዓለም በመጣ ጊዜ “ኹሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይኾናሉ የሚል ጽሁፍ በነቢያት መጽሓፍ ይገኛል። እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ኹሉ ወደእኔ ይመጣል።” ሲል በተናገረው ቃሉ፡ ያን ትንቢቱን አጽንቶታል። ማጽናት ብቻ አይደለም። አይኹድ፡ “ይኽ ሰው ማንም ሳያስተምረው መጽሓፍትን እንዴት ያውቃል?” ብለው ይደነቁ ነበር። ጌታችን እየሱስም ‘ትምህርቴስ ከላከኝ እንጂ ከእኔ አይደለችም አላቸው።” ባለው የምሥራች ቃሉ፡ ያው ትንቢት በእርሱም ሰውነት ተፈጽሞና ተከስቶ ይታይ ዘንድ ለጣፋጩ ፍሬያማነቱ አብቅቶታል።
“አስተማሪያችሁ አንዱ እርሱ የሰማዩ አባታችሁ ስለኾነ፤ ለእናንተ በምድር ላይ አስተማሪ አይኑራችሁ። እናንተማ ኹላችሁም፡ ወንድማማች ናችሁ” ባለው ቃሉ መሠረት፡ የሚካሄደው በመንፈስ ቅዱስ ስለኾነ፡ አስተማሪው እራሱ እግዚአብሔር ነው። የማስተማሪያው መጻሓፍት፡ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከኾነ ኢትዮጵያዊ ልቦና የሚፈልቁ የእግዚአብሔር ናቸው። ተማሪዎቹም፡ በግልጽ እንደሚታየው፡ ሰው ነው። መካነ አእምሮ ወይንም ትምህርት ቤቱ፡ ህያው የኾናው ራሱ የሰውነት አካል ነው። መጻፊያውና የማስተማሪያው መሳሪያዎች፡ የመንፈስ ቅዱስ ጣቶች ናቸው። ገበታው፡ የሰው ልብ፡ ሰሌዳውም የሰው ህሊና ነው። የሚነገሩት የሚደመጡትና የሚጻፉት ፊደላትና ቃላት የእግዚአብሔር ናቸው። ማቴዎስ ምዕራፍ ፳፫ ከቁጥር ፮-፰.
ኢትዮጵያዊነታችን የተመሠረተው፡ በእግዚአብሔር ስለኾነ፡ እግዚአብሔርም፡ እውነት ስለኾነ፡ እኛ፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊያን፡ የምናስበው፤ የምንናገረውና የምናደርገው ኹሉ፤ ከዚች እውነት የተለየ አይደሎም። መመሪያችን፡ ሃይማኖታችን ነው። ይህንኑም ሃይማኖት፡ ጥንቱኑ፡ እግዚአብሔር፡ ከአዳምና ሔዋን ጀምሮ፡ ራሱ፡ በነፍሳችን አማካይነት ባስተማረን፤ በየልቦናችን ጽላት ላይ በጻፈልንና በየሕሊናችን መዝገብ ውስጥ ባሳደረለን፡በቅዱሱ ኪዳን ተቀብለነው፤ አውቀነውና አምነንበት ኖረናል፤ በመደምደሚያውም፡ በኢየሱስ ክርስቶስና በድንግል ማርያም፡ እውን ኾኖልን፡ ለፍጹምነት በቅቶልናል፤ ስለዚህ፡ ሃይማኖታችን፡ ከፈጣሪ እንደተገኘ ጸጋና ሃይል እንጂ፡ ዓለማውያንና ሥጋውያን አዋቂዎች፡ አስበውና አዘጋጅተው በሚያቀርቡት መጻሓፍት የተሞረኮዘ አይደለም። አይኾንምም። ስለዚኽ፡ ለማንኛውም የጽሑፍ ሥራችን ዋናውና ብቸኛው ምንጭ፡ መጽሓፍ ቅዱስ ነው።