ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ ከየት ተገኘ?
“ኢትዮጵያዊነት” ከሚለው ቃል ጋር፡ የጥሬ ዘርና የምሥጢር፥ የዘይቤና የትርጉም ተዛምዶ ያላቸው፡ በዓለም ሕዝቦችና ቋንቋዎች ዘንድ የታወቁ፡ አንዳንድ ይፋ ቃላት አሉ። ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፦
፩ኛ. “ኢትዮጵያ” ለማለት፡ “ጦብያ” የሚለው ትውፊታዊ፥ ምጽሓፋዊና ሕዝባዊ ቃል፤
፪ኛ. ጥንታውያን የዓለም ፈላስፎችና ደራስያን፡ የኢትዮጵያን፡ ምድራዊት ገነትነትና የኢትዮጵያውያንን መልአካዊ አኗኗር፡ በመንፈስ በማየትና በዜና በመስማት፡ የኢትዮጵያን፡ ማንነትና የኢትዮጵያዊነትን ምንነት፡ በየጽሑፋቸው ለመግለጽ ይጠቀሙበት የነበረው፥ ይህን የመሰለውን ሕይወት፡ በምድር ላይ ለመፍጠርና ለማግኘት ይቻላል በሚል እምነት፡ የሰው ልጅ፡ ዛሬም እየተጠቀመበት የቀጠለው፡ “ዩቶፒያ” (Utopia) የሚለው የቅርስ ቃል፤
፫ኛ. ጥንት፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፡ ምድራዊ ክልል ውስጥ ይኖር የነበረ፡ ዓሣ በላተኛ ሕዝብ፡ ተለይቶ ይጠራበት የነበረው “ኢትዮፓጊ” (Ichthyophagi) የሚለው የስያሜ ቃል፤
፬ኛ. ዕብራዊያን፡ በዕብራይስጥ ቋንቋቸው፡ “ኢትዮጵያ” ወይም “ኢትዮጽያዊ” ለማለት የሚጠቀሙበት፡ “ኵሽ” የሚለው የተጸውዖ ቃል፤
፭ኛ. ዓረቦች፡ “ኢትዮጵያ” ወይም “ኢትዮጽያዊ” ለማለት የሚጠቀሙበት፡ “ኻበሽ” ወይም “አበሽ” የሚለው የዓረብኛ መጠሪያ ቃል፤
፮ኛ. እንግሊዞች፡ ይኽን የዓረብኛውን ቃል ቆልምመው፡ ወይም “አቢስ” የተባለው የነገድ አባት ዝርያዎች ናቸው ለማለት የተጠቀሙበት፡ “አቢሲንያ” የሚለው መለያ ቃል፤
፰ኛ. በመጨረሻም፡ ኢትዮጵያውያን፡ በቅዱሱ ኪዳን ሃይማኖታቸው መሠረትነት በሠመረው የኅብረተሰብአዊነት ህልውናቸው የሚታወቁበትና የሚጠሩበት፡ “ዐምሓራ” የሚለው የውህደት ስም።
“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል፡ “ኢትዮጲስ” ከሚለው፡ ከመጀመሪያው መልከ ጼዴቅ፡ በውህደት ለበቀለው፡ የዘር ግንድ ከተሰጠው ስም የተገኘ አጠራር ሲኾን፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፡ ጥንታውያኑ የዓለም ሕዝቦች፡ ይልቁንም ግሪኮች፡ ከሌሎቹ ነገዶች የመልክ ቀለማት፡ የተለየና የታወቀ የኾነውን፡ የኢትዮጵያውያንን የመልክ ዓይነት፡ ራሱን አስችለው፡ ለመጠቆም ሲሉ፡ በዚሁ፡ “ኢትዮጲስ” (Aethiops) በሚለው ቃል የተጠቀሙ መኾናቸውን፡ ሕያው የኾነው፡ የኢትዮጵያውያን ትውፊት፡ በአጽንዖት ያመለክታል። በዚህ የጎላ ቀለም፡ ተለይቶ የታወቀውን፡ ይህን ኢትዮጵያዊ ባሕርይና ገጽታ ያለው መኾኑን፡ አምላካዊው የትንቢት ቃል፡ እንዲህ ሲል፡ በሥዕላዊ አቀራረብ አሳምሮ በማስረዳት፡ በነቢዩ በኤርምያስ አንደበት፡ ገልጾታል፦ “በውኑ፥ ኢትዮጵያዊ፡ መልኩን፥ ወይስ ነብር፡ ዝንጕርጕርነቱን ሊለውጥ ይችላልን?” (ኤር. ፲፫፥ ፳፫)
(ለተጨማሪ ማብራሪያ ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ! ከገጽ ፵፮ ጀምሮ ይመልከቱ)