የብሉይ እና የአዲሱ ኪዳናት ጽላትና ታቦታት የተለያዩ ናቸው?
አዎን! የተለያዩ ናቸው።
ኹለቱን፡ የብሉዩን ኪዳን ጽላት ተክቶ፡ በአዲሱ ታቦት ውስጥ የተቀመጠው፡ አዲሱ፡ አራት ማዕዘን ነጠላ ጽሌ፡ በላዩ ተቀርጾ የሚታየው ጽሑፍ፡ እንደቀደሙት ጽላት፡ አሥሩን ትእዛዛት የያዘው፡ የእግዚአብሔር ቃል ሳይኾን፡ ያ ቃል፡ በድንግል ማርያም ማኅጸን፡ ሰው መኾኑን ለማሳየት፡ በመኻል፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ኾኖ፡ በቀኝ፡ የቅድስት ድንግል ማርያም፥ በግራ፡ የወንጌላዊው ዮሓንስ ሥዕሎች፥ ዙሪያውንም፡ የእግዚአብሔር፡ የአምላክነቱ ስሞች ተጽፈውና ተሥለው ነው።
ያ፡ ታቦት የሚገኝበት ቤተ መቅደስ፡ በጌታ ወይም በእመቤታችን ስም እንደኾነ፡ ስማቸው፥ አለዚያ፡ መታሰቢያነቱ፡ ለነቢይ፥ ለሓዋርያ፥ ለጻድቅ፥ ለሰማዕት ወይም ለመልአክ ከኾነ፡ የዚያ ቅዱስ ስም፡ “ዝ ጽላት፡ ዘቅዱስ እከሌ” ተብሎ፡ ከጀርባው ይቀረጽበታል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፡ በዚያ፡ በመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ጽሌ ዓይነት፡ ነገር ግን አራት ማዕዘን ኾኖ፡ በዕብነ በረድ፡ ወይም በማይነቅዝ የእንጨት ወገን፡ በተለያየ ቅጽና ቅርጽ እየተዘጋጀ፥ እየተራባና በተገቢው ሥርዓተ ጸሎት እየተባረከ፥ ታቦት በተባለውም፡ የእንጨት ሳጥን ውስጥ በክብር እንዲቀመጥ እየተደረገ፡ ሲሠራበት ኖርዋል። ከዚኽ በኋላ፡ ይኽን የመሰለውን ጽላትና ታቦት፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፡ ለሰው ልጆች ባስገኘው ዘለዓለማዊ ትድግናው አማካይነት፡ የሚወርዱትን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች፡ ወደምእመናን ለማስተላለፍ የሚያስችሉት ምሥጢራትና ሥረዓታት በሚፈጸምበት፡ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መቅደስ ባለው መንበር ውስጥ ያኖሩታል።
በብሉይ ኪዳን እንደነበረው ኹሉ፡ የአዱሱ ኪዳኑም ጽሌ፡ ወይም በልማድ እንደሚባለው፡ ጽላቱ፡ የኢየሱስ ክርስቶስ፥ ታቦቱ ደግሞ፡ የቅድስት እናቱ፡ የድንግል ማርያም ምሳሌ የመኾኑ ምሥጢር፡ ሳይቃወስ ቀጥሏል።
(ለተጨማሪ ማብራሪያ ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ! ከገጽ ፹፩ ጀምሮ ይመልከቱ)